'ትግራይ መጠበቅ አትችልም' የድረገጽ የሰብዓዊ ድጋፍ ማሰባሰቢያ መርሃግብር ተካሄደ
ትግራይ ካንት ዌይት ወይም ‘ትግራይ መጠበቅ አትችልም’ ሲሉ ነዋሪነታቸውን በዚህ በዩናይትድ ስቴትስ ያደረጉ የትግራይ ምሁራን እና ተወላጆች በትላንትናው ዕለት በዋሽንግተን ሰዓት አቆጣጠር ከእኩለ ቀን እስከ እኩለ ሌሊት ድረስ ክለብ ሃውስ በተሰኘ የውይይት መተግበሪያ ላይ በመገናኘት ጥናታዊ ጽሆፎችን በማቅረብ፣ በጎ ፈንድ ሚ እና በሌሎች የገንዘብ ማሰባሰቢያ መንገዶች በመጠቀም የገቢ ማሰባሰቢያ አድርገዋል፡፡
በተጨማሪም የተለያዩ ጨረታዎችን እና የሙዚቃ ዝግጅቶችን በማካሄድ ከ12 ሰዓታት በላይ ቆይተዋል፡፡በመርሃግብሩ ላይ የሙዚቃ ዝግጅቶች በገቢ ማሰባሰቢያነት ለጨረታ የቀረቡ ጌጣጌጦች፣ የትግራይ ክልል ባንዲራ፣ ሹራቦች፣ የአፍ እና የአፍንጫ ጭንበሎች እና ስዕሎች የተጫረቱበት እንዲሁም ሰፋ ያለ የፓነል ውይይት ተካሂዷል፡፡ በዋናነት በውይይቶቹ ላይም የትግራይ ልማት ማሕበራት ከዚህ ቀደም ያበረከቷቸው አስተዋጽኦዎች፣ የመገናኛ ብዙሃን ቅኝት ፣ የትግራይ ባህልና እና ታሪክን እንዲሁም ጦርነቱ በሌሎች የግብረሰናይ እንቅስቃሴ የሚሳተፉ የውጭ ሃገር ዜጎች ዓይን የተቃኘበት ነበር፡፡
የመርሃግብሩ አስተባባሪ የሆኑት ዶ/ር ሙሉጌታ ገብረእግዚአብሔር የደቡብ ካሮላይና ግዛት በሜዲካል ዩኒቨርስቲ መምህር ሲሆኑ በመርሃግብሩ ዙሪያ ከአሜሪካ ድምጽ ጋር ቆይታ አድረገዋል፡፡