Friday, November 13, 2020

ልመናዎች

 ልመናዎች

አባ ተስፋማርያም ባራኪ 

አቤቱ ፈጣሪ ጌታ፣
ምስጋና ይድረስህ ጥዋትና ማታ፣
በኃጢአት ሰው እንዳይንገላታ፣
ተፈትኖ በሰይጣኑ ወስላታ፤
አፍስስለት የጸጋህን ስጦታ፣
መንፈሱ በእምነት እንዲበረታ፣
ሳይሸበር እንዲኖርም በደስታ፣
ሰላምህ ይንገሥልን በሁሉም ቦታ፣
ጥላቻ በዝቶ ሰው እንዳይማታ፣
ፍቅር ይብዛልን እንዳይሆን ዝምታ፣
ክፋት በዝቶ ሰው ከገነት እንዳይገታ፣
ምሕረትህን ስጠው ባንተው ችሎታ፣
ወደ ገሃነም እንዳይወርድ ቀጥታ፣
አንተው ሁንለት ኃያሉ መከታ፣
እየፈወስከው ከኃጢአቱ በሽታ


አንተ ነህና የሁሉም አባት፣
ሰው እንዲኖር በአንድነት፣
ነፃ አድርገው ከጥላቻ ኃጢአት፣
እንዳይገባ ወደ ገሃነመ እሳት፣
እንዳይኖርም በሰይጣን ባርነት፣
ታስሮ በትዕቢቱ ሰንሰለት፣
ለዘለዓለመ ዓለም ከማይፈታበት፣
ተገዝቶ ከሰማያዊው ገነት።
ባንተው ታልቁ ቼርነት፣
መልሰው ወደ ንስሐና ጸሎት፣
አሳየውም ያንተውን ምሕረት፣
እንዳይቀጣ በዘላለማዊው ሞት፣
አንተ ነህና ለሰው የዘላለም ሕይወት።


አቤቱ አንተ ነህና የዓለም ፈጣሪ፣
ሰው ሁሉ እንዲሆን የስምህን አክባሪ፣
እንዲያውቅም መሆንህን መሓሪ፣
እንደሌለም ካንተ በቀር ሌላ መሪ፣
የተፈጥሮ ሁሉ አስተዳዳሪ፣
ሳይኖርህ አንድም አማካሪ፣
ሳይገኝልህም ማንም ተወዳዳሪ፤
ዲያብሎስ ብቻ የጠብ ጫሪ፣
በትዕቢቱ በጣም ፎካሪ፣
በደካማው ላይም ወራሪ፣
ሰው እንዲሆን ክፋት-ሠሪ፣
በእምነቱም በጣም ተጠራጣሪ፣
ወይም ደግሞ በፍጹም አክራሪ፣
አንተ ነህና ለሰው ጠበቃና ተከራካሪ፣
የእውነትንም ሁሉ አስተማሪ፣
በጸጋ ላይ ጸጋን አበዳሪ፣
ሰው እንዳይሆን የውሸት አውሪ፣
ይልቅስ እንዲሆን የአምላክ ፈሪ፣
እንዲሆንም ሰውን ሁሉ ኣፍቃሪ፣
ባርከው እንዲሆን የትእዛዛትህን አክባሪ፣
ለዘላለምም የምስጋናህን ዘማሪ።


አቤቱ ጸሎታችንን ስማ፣
ከገጠር እስከ ከተማ፣
ኢትዮጵያዊው ሁሉ እንዲስማማ፣
እንዲኖረውም አንድ አላማ፣
ለወገኑና ለሀገርቷ የሚስማማ፣
እየተመራ ባንተው ፍቅር አርማ፣
ሕይወቱ በሰላምና ጸጋ እንዲለማ፣
እንዲኖረውም መንፈሳዊ ግርማ፣
እንዲዘምርልህም የምስጋናን ዜማ፣
እንደ አባታችን አቡነ ሰላማ፣
ኢትዮጵያን ያወጣት ከአረማውነት ጨለማ።

No comments:

Post a Comment

Note: Only a member of this blog may post a comment.